የሕግ ማስከበር ዘመቻው በጥንቃቄና በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ መንግስት ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ያሳያል – የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የሕግ ማስከበር ዘመቻው በከተሞች ላይ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ መንግስት ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት እንደሚያሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ተገኝተው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት መንግስት ንጹሃን የትግራይ ተወላጆችና ከፍተኛ ወጪ የተደረገባቸው መሰረተ ልማቶች የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቁን አድንቀዋል የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ገበያነሽ ነጋሽ መከላከያ ሠራዊቱ ስትራቴጂካዊ በሆነ ስልት ንጹሃን ሳይጎዱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያደረገው ተጋድሎ እንደሚያስመሰግነው ተናግረዋል። ጁንታው ለሕዝብ ደንታ ስለሌለው በተለይ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ጭምር በመጠቀም ሊያደርሰው የነበረው ጥፋት መክሸፉ የሠራዊቱን ጥንካሬ እንደሚያሳይ ገልጸዋል። መንግስት ለሕዝቡ የሚያስብና አርቆ አሳቢ በመሆኑ ሊደርስ የነበረውን ጉዳት በጥበብና በዘዴ ማክሸፍ ችሏል ብለዋል። ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ነሂማ አህመድም የወይዘሮ ገበያነሽን ሀሳብ ይጋራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ፅንፈኛው ቡድን ንጹሃንን መግደልና ማሰቃየት ለረጅም ጊዜ ሲከውነው የነበረ ተግባሩ ነው። ይህ ድርጊት አገር የመምራት ዕቅድ ካለው መሪም ሆነ ድርጅት የማይጠበቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ የቡድኑን አደገኝነት በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደረገ ነው ብለዋል። “መሰረተ ልማቶች የሕዝብ መጠቀሚያ እንደመሆናቸው በጁንታው ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ በማደራጀት የክልሉን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ይገባል” ያሉት ደግሞ አቶ መስፍን መሸሻ ናቸው። በምክር ቤቱ ብቸኛዋ የትግራይ ክልል ተወካይ ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ በበኩላቸው መንግስት የትግራይ ሕዝብ በጽንፈኛው ቡድን የከፋ ጉዳት እንዳይደርስበት ኃላፊነት የተሞላበት ጥንቃቄ አድርጓል ብለዋል።ለጽንፈኛው ቡድን በሠላም እጁን እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ ለሕዝቡ ያለውን ክብር ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል።


ጁንታው በሕዝብ ንብረት የተገነባን መሰረተ ልማት አፈራርሶ መሸሹ “እታገልለታለሁ” ለሚለው ሕዝብ እንኳን የማያስብ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው ይላሉ ወይዘሮ ገበያነሽ። አቶ መስፍንም የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጁንታው አፈናና ጭቆና ሲደርስበት ነበር ብለዋል። የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የሶስት ሣምንታት የሕግ የማስከር ዘመቻውን በንጹሃን ዜጎችና ትላልቅ የመሰረተ ልማት ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄ ከውኖታል። በተቃራኒው ጽንፈኛው ቡድን ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶችና አውሮፕላን ማረፊያዎችን ጨምሮ ለዜጎች መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን አውድሟል።

0 0 vote
Article Rating

You may also like...

Subscribe
Notify of
guest
0 Comments
Inline Feedbacks
View all comments
0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x