የምክር ቤቱ ውሎ የኢትዮጵያዊያን ሃሳብ የተነሳበት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የጀመሩትን መጨረስ እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው

አዲስ አበባ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የዛሬው የምክር ቤቱ ውሎ “የመላው ኢትዮጵዊያን ሃሳብ የተነሳበት፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩም የጀመሩትን መጨረስ እንደሚችሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳዩበት ነው” ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ ገለፁ።

ሕወሃት ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ መጥፎ ምሣሌ በመሆኑ ሊሰረዝና በአሸባሪነት ተፈርጆ ሊወገድ የሚገባው ድርጅት ነው ብለዋል። የዛሬውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያና የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ወንድሙ ኢብሳ ምክር ቤቱ በወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩን መጥራቱ ተገቢ መሆኑን፣ የአባላቱ ጥያቄዎችም የመላ ኢትዮጵያዊያንን ሃሳብ ያካተቱ እንደሆኑ ገልጸዋል። ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ብሔርና አገራዊ ማንነታቸው የማይጋጭባቸው ናቸው ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት አቶ ወንድሙ ስልጣን እንጂ ኢትዮጵያን የሚጠሉና አገራቸውን ለማፍረስ የሚታትሩ ቡድኖች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ከነዚህም መካከል ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በ1983 ዓ.ም የአገር መከላከያ ሠራዊትን ያፈረሰውን፣ ወደቦቿን ያሳጣውን፣ ሕዝቦችንም እርስ በርስ በማጋጨት ለ27 ዓመት በስልጣን የቆየውን ህወሓት ለአብነት ያነሳሉ። በ2010 ዓ.ም ከማዕከላዊ መንግስት በሕዝብ ትግል የተገፋው ህወሓት ለ27 ዓመት ለፈፀመው በደል በይቅርታ ቢታለፍም የማይገባቸውና ከባህል ባፈነገጠ ነውረኛ ተግባር የተዘፈቁ ሰዎች ስብሰብ በመሆኑ ከስህተቱ እንዳልተማረ ይናገራሉ።


በየትኛውም የመንግስት ምስረታ ታሪክ በርካታ ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ የሚገልጹት አቶ ወንድሙ፤ የሕይወት ግብር ገብሮ አገር በሚጠብቅ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ግፍ ግን እጅግ የከፋ ስለመሆኑ ያነሳሉ። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ ማስከበር ሂደቱን አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያም ‘ከንግግር በላይ የጀመረውን መጨረስ እንደሚችል ለመጠበቅ የማይቻል ትዕግስት ማድረግ እንደሚችል ራሱን የቻለ መፅሃፍ ለፓርላማውም ለኢትዮጵያ ሕዝብም አቅርቧል’ ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእውቀትና በጥበብ የበለጧቸው የጽንፈኛው ቡድን አባላት ባላቸው የበታችነት ስሜት ለውጡን ሲያደናቅፉ እንደነበር ገልጸው፤ በሕግ ማስከበር ሂደቱ መቀሌ የተያዘችበትን ሂደት አድንቀዋል። በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በፈጸመው ቡድን ላይ ሕግ ለማስከበር የተወሰደው አርምጃ ንጹሃንን ሳይጎዳ በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ መከወኑ ብሎም የትግራይን ሕዝብ ከጁንታው ሳይሆን ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ማሳለፍ መቻሉ ትልቅ ድል እንደሆነም ገልጸዋል። ይህም የመንግስትን ተቀባይነት የጨመረ አጋጣሚ መሆኑን ነው የተናገሩት። የመቀሌው ድል በአገር ውስጥ ወንጀለኛ ቡድን ላይ ከመደረጉ በቀር በጦር ሠራዊቱ የተሰራው ስራ እንደ አድዋ፣ ባድመና ካራማራ የሕዝብ አንድነት የታየበት አኩሪ ድል መሆኑንም አክለዋል። አቶ ወንድሙ በምክር ቤቱ በተደጋጋሚ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ‘ሕወሃትና ኦነገ ሸኔ ለምን በአሸባሪነት አልተፈረጁም’ የሚለውን እንደሚጋሩትም ገልጸዋል። ሕወሃት ከ60 ሺህ ያለነሰ የትግራይ ወጣት ካለቀበት ትግል በተጨማሪ በ27 ዓመታት የስልጣን ቆይታው ከደርግ የባሱ ጭቆና፣ አፈናና ግድያ ማድረሱን ይገልጻሉ። ጽንፈኛው የሕወሃት ቡድን በሕገ መንግስቱ መሰረት በፈጸማቸው ወንጀሎችና ባፈሰሰው ደም መወገድ ያለበት ድርጅት እንደሆነ አመልክተዋል። ‘የካቲት 11 የተወለደው ህወሓት ሕዳር 19 ሞቷል’ ያሉት አቶ ወንድሙ ከሕግ፣ ከታሪክ፣ ከባሕልና ከሞራል አንጻር ቡድኑ በፓርላማ በአሸባሪነት ተፈርጆ ከፖለቲካው መሰናበት ያለበት ነው ብለዋል። የህወሓት መወገድ እንደ እርሱ በየሰፈሩ ጁንታ መሆን የሚያምረው ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርጋል ነው ያሉት።

0 0 vote
Article Rating

You may also like...

Subscribe
Notify of
guest
0 Comments
Inline Feedbacks
View all comments
0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x